face
  •   
  •  


እጅግ በጣም ርኅሩሁ በጣም አዛኙ አላህ . .

‹‹እጅግ በጣም ርኅሩሁ፣በጣም አዛኝ፣በጎ አድራጊ፣ቸር፣በጣም ለጋሽ፣ርኅሩህ፣ሰጪ›› እነዚህ ስሞች ትርጉማቸው ተቀራራቢ ሲሆን፣ሁሉም በእዝነት በርኅራሄ በቸርነትና በለጋስነት የሚገለጽ፣ቸርነትና ችሮታው የሰፋ፣ደግነቱ ጥበባዊ ውሳኔው በሚጠይቀው ሁኔታ መላውን ፍጥረተ ዓለም የሚያዳርስ መሆኑን ያመለክታሉ። እዝነቱና ርኅራሄው ሁሉን አቀፍ ቢሆንም፣የምእመናን አገልጋዮቹ እጣ ፈንታ ግን በተለይ ከፍተኛና የተሟላ ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ችሮታየም ነገሩን ሁሉ ሰፋች፤ለነዚያም ለሚጠነቀቁ፣ . . በእርግጥ እጽፋታለሁ።›› [አልአዕራፍ፡56] ጸጋዎችና በጎ ነገሮች ሁሉ የአላህ ﷻ ችሮታ፣የእዝነቱና የደግነቱ ውጤቶች ናቸው። የዱንያና የኣኽራ ትሩፋቶች ሁሉ ምንጭ የአላህ እዝነትና ችሮታው ነው።

እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩሁ በጣም አዛኙ አላህ ነው . .

በራሱ ላይ እዝነትን ጽፏል። እዝነቱ ከቁጣው ቀድሟል። እዝነቱና ችሮታው ለነገሮች ሁሉ የተዘረጋና ተደራሽ ነው . . ‹‹የአላህ ችሮታ ከበጎ አድራጊዎች ቅርብ ነውና።›› [አልአዕራፍ፡56]

‹‹እርሱ በጣም አዛኙ እጅግ በጣም ርኅሩሁ ነው›› እርሱ ከእናቶቻችን ይበልጥ ለኛ አዛኝ የሆነ ጌታ ነው። ረሱልﷺ ሕጸን ልጇን የምታጠባን እናት በማስመልከት እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ይህች ሴት ልጇን ወደ እሳት ትወረውራለች ብላችሁ ትገምታላችሁ?›› ሲሉን አለመወርወር እየቻለች አታደርገውም አልናቸው። ‹‹እንግዲያውስ ይህች ለልጇ ከምታዝነው ይበልጥ አላህ ለባሮቹ አዛኝ ነው።›› አሉ። (በቡኻሪ የተዘገበ)

‹‹እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩሁ በጣም አዛኙ ነው››

ለፍጥረታቱ ሁሉ ያዝናል፣ይራራላቸዋል፤ለምእመናን ባሮቹ ግን የተለየ እዝነትና ርኅራሄ አለው። ‹‹ለአማኞችም በጣም አዛኝ ነው።›› [አልአሕዛብ፡43]

‹‹እርሱ በጣም አዛኙ ነው›› . . ከእዝነቱና ከርኅራሄው መካከል ታላቁ ሙሐመድንﷺ ለዓለማት እዝነትና ለሰው ልጆች ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ጥቅሞቻቸውን እውን ለማድረግ መሪ ብርሃን አድርጎ መላኩ አንዱ ነው።

‹‹እርሱ በጣም አዛኙ ነው›› . .እዝነቱንና ችሮታውን ከርሱ በስተቀር ማንም ሊያግደው፣ከርሱም በስተቀር ማንም ሊልከው አይችልም። ‹‹አላህ ለሰዎች ከችሮታ የሚከፍታት ለርሷ ምንም አጋጅ የላትም፤የሚያግደውም ከርሱ በኋላ ለርሱ ምንም ለቃቂ የለውም፤እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው።›› [ፋጢር፡2]

እነሆ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩሁ በጣም አዛኙ አላህ ነው . .

በጣም ለጋሱ በጣም ቸሩ አላህ . .

እርሱ በጣም ለጋሱ በጣም ቸሩ አላህ ነው . .

የጸጋዎች ለጋሽ ሆይ! . . የተስፋዎች ለጋሽ አንተ ሆይ! . . የደግነት ለጋሽ አንተ ሆይ! . .

ወዶ መቀበልን ለግሰኝ . . ደህንነትን ለግሰኝ . . ተድላ ደስታና እዝነትን ለግሰኝ . .

በቸርነትህና በልገሳህ ጎብኘን፤አንተ የችሮታ የትሩፋት፣የደግነትና የልገሳ ባለቤት ነህና . . ‹‹(እነሱም ይላሉ)፦ ጌታችን ሆይ! ቅኑን መንገድ ከመራኸን በኋላ ልቦቻችንን አታዘንብልብን፤ከአንተ ዘንድ የኾነን ችሮታም ለኛ ስጠን፤አንተ በጣም ለጋስ ነህና ።›› [ኣል ዒምራን፡8],‹‹አላህ ቸር ነውና ቸርነትንና የላቀ ስነምግባርን ይወዳል፤ወራዳውን ይጠላል።›› (በትርምዚ የተዘገበ)

‹‹በጣም ለጋስ›› . . ለሻው ሰው ይለግሳል፤ያሻውን ሰውም ይከለክላል።

‹‹በጣም ቸር›› ቸርነቱና ስጦታው ገደብ የለውም፤ችሮታው ከርሱ በቀር አጋጅ የለውም። ለነገሮችም እንዲህ ይላል፦ ‹‹ኹን፤ወዲያውም ይኾናል።›› [አልበቀራህ፡117]

‹‹በጣም ለጋስ›› . . ቁሳዊ ሲሳይና ሕሊናዊ ሲሳይ ይለግሳል፤በችሮታውና በደግነቱ ይሰጣል።

ከልገሳዎቹ መካከል አላህ ለባሪያው አእምሮው ውስጥ የሚከፍትለት መልካም ሃሳቦች፣ጠቃሚ ግንዛቤዎች፣ዕውቀት፣ቅን መመሪያ፣ስኬታማነትና የዱዓው ተቀባይ መሆን . . ይገኙበታል። እነዚህና ሌሎቹም አላህ ﷻ ለብዙ ሰዎች የቸራቸው ሕሊናዊ ሲሳይ ናቸው።

‹‹በጣም ለጋስ›› . . በጣም ለጋስ ነውና ይሰጣል፣ይነሳል። ዝቅ ያደርጋል፣ከፍ ያደርጋል። ይቀጥላል፣ይቆርጣል። በጎው ሁሉ በርሱ እጅ ነው፤እርሱም በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው።

እርሱ በጣም ለጋሱ በጣም ቸሩ አላህ ነው . .

ችሮታ ሰፊው አላህ . .

እርሱ ችሮታ ሰፊው አላህ ነው . . ‹‹አላህ ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነውና።›› [አልበቀራህ፡115]

‹‹ችሮታ ሰፊው›› . . የተጠየቀውንና የተለመነውን ሁሉ ለመስጠት ብቁ የሆነ በጣም ቸር ነው።

‹‹ችሮታ ሰፊው›› . . በባሕርያቱ ምሉእ .. በስሞቹ ታላቅ፣ምስጋና እና ውዳሴው ገደብ የሌለው፣ኃያልነቱ፣ግዛቱ፣ሥልጣኑ፣ትሩፋቱ፣ቸርነቱና ደግነቱ የሰፋና እጅግ የገዘፈ ችሮታ ሰፊ።

‹‹ችሮታ ሰፊው›› . . በስጦታው፣በበቂነቱ፣በዕውቀቱ፣በከባቢነቱ፣በጥበቃውና በቅንብሩ ለፍጥረታቱ ሁሉ የሰፋ ነው።

‹‹ችሮታ ሰፊው›› . . ድምጾችን ሁሉ የሚሰማ፣ቋንቋዎች የማይምታቱበት ችሮታ ሰፊ።

‹‹ችሮታ ሰፊው›› . . ለባሮቹ እርሱን ማምለክን የገራላቸው፣ሃይማኖትን ቀላልና ምቹ ያደረገ፣ነገሮችን ያሰፋላቸው ችሮታ ሰፊ ጌታ።

እርሱ ችሮታ ሰፊው አላህ ነው . .

ወዳዱ አላህ . .

እርሱ ወዳዱ አላህ ነው . . ‹‹እርሱም ምሕረተ ብዙ ወዳድ፣ነው።››[አልቡሩጅ፡14]

አላህ ባሮቹን ወዳድ ነው . . ይወዳቸዋል፤ያቀርባቸዋል፤ያስወድዳቸዋል፤በጎ ሥራቸውን ከነርሱ ወዶ ይቀበላል . . ‹‹የሚወዳቸውንና የሚወዱትን።›› [አልማኢዳህ፡54]

አላህ ሰዎች ይወዷቸው ዘንድ ተወዳጆች ስለሚያደርጋቸው፣በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትንና ተቀባይነትን ያገኛሉ።

‹‹በጣም ወዳዱ›› . . ነቢዮቹን፣መልእክተኞቹንና ተከታዮቻቸውንም የሚወድና የሚወዱት፤ከምንም በላይ እነርሱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ፣ልቦቻቸው በርሱ ፍቅር የተሞላ፣ምላሶቻቸው በርሱ ውዳሴ የሚርገበገቡ፣ውስጣቸው በሁሉም ገጽታ በርሱ ፍቅር ለርሱ ፍጹም በመሆንና ወደርሱ በመማለስ የተጠመደ።

‹‹በጣም ወዳዱ›› . . በጣም ቅርቡና ለባሮቹ በጎ በጎውን የሚወድ በጣም ወዳዱ ነው።

‹‹በጣም ወዳዱ›› . . ባሮቹ ይወዱታል፤ከርሱ ጋር መገናኘትንም ይናፍቃሉ። በነቢዩﷺ ሐዲሥ ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን፦ ‹‹አላህን መገናኘት የወደደን ሰው አላህ ከርሱ ጋር መገናኘትን ይወዳል።›› (በቡኻሪ የተዘገበ)

‹‹በጣም ወዳዱ›› . . ልቦናህን እንድታጠራ፣ከጥላቻና ከቅያሜ እንድታጸዳው፣የጥላቻን ቆሻሻ በፍቅር ውሃ እንድታጥብ፣የቅናትና የምቀኝነትን እሳት በፍቅርና በውዴታ በረዶ እንዲታጠፋ ያዘሃል።

እርሱ በጣም ወዳዱ አላህ ነው . .

ሕያው፣ሁሉን ነገር አስተናባሪው አላህ . .

እርሱ ሕያው፣ሁሉን ነገር አስተናባሪው አላህ ነው . . ‹‹ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤(እርሱ) ሕያው፣ሁሉን ነገር አስተናባሪ ነው።›› [ኣል ዒምራን፡2]

እርሱ የሁሉም ነገር አስተናባሪው አላህ ነው . . ‹‹ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤(እርሱ) ሕያው፣ሁሉን ነገር አስተናባሪ ነው።›› [ኣል ዒምራን፡2]

‹‹ሕያው፣የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› ሕያውነቱ ፍጹም ምሉእ የሆነ፣ራሱን በራሱ የተብቃቃ፣የሁሉም ነገር አስተናባሪ፣የሰማያትና የምድር ነዋሪዎችን አስተናብሮ የሚያኖር፣ሲሳይአቸውንና ነገሮቻቸውን ሁሉ የሚያቀነባብር። ‹‹ሕያው››የርሱነቱን (የዛቱን) ባሕርያት ሁሉ ያጠቃለለ ‹‹ሕያው››፣ባሕርያቱን ሁሉ ያካተተ በራሱ የተብቃቃ።

‹‹ሕያው›› . . ምሉእና እውነተኛው ሕያውነት፣ ለሕልውናው ምንምና ማንም አስፈላጊው ያልሆነ፣ከርሱ ውጭ ላሉት ህልውናዎች ሁሉ የግድ አስፈላጊ የሆነ . . ከርሱ በስተቀር ሁሉም ነገር ጠፊ የሆነ ሕያው።

‹‹የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› . . ራሱን የቻለ፣ ከርሱ በቀር ካሉት ሁሉ ፍጹም የተብቃቃ።

‹‹የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› . . የሁሉም ነገር አቀናባሪና አስተናባሪ፣የነፍሶች ሁሉ ተቆጣጣሪና ጠባቂ፣የሥራዎቻቸው፣የሁኔታዎቻቸውና የንግግሮቻቸው፣የበጎ ተግባራቸውና የእኩይ ሥራዎቻቸው መዝጋቢ፣በኣኽራ ለሁሉም እንደሥራቸው የሚሰጥ።

‹‹የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› . . ባሮቹ የሠሩትን ለክቶ የሚቆጥር።

‹‹የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› . . የእያንዳንዱን ፍጡር ሕይወት፣ሲሳይና ሁኔታዎች የሚያስተናብርና ጉዳዮቻቸውን የሚያቀናብር።

‹‹ሕያው፣የሁሉም ነገር አስተናባሪው›› ማለፍ የማያገኘው ዘለዓለማዊ ቀሪ።

እርሱ ሕያው፣ሁሉን ነገር አስተናባሪው አላህ ነው . .

ጠጋኙ አላህ . .

እርሱ ኃያሉ ጠጋኙ አላህ ነው . . ‹‹እርሱ አላህ ነው፤ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ንጉሡ፤ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣የሠላም ባለቤቱ፣ጸጥታን ሰጪው፣ባሮቹን ጠባቂው፣አሸናፊው፣ኃያሉ፣ኩሩው ነው። አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ።›› [አልሐሽር፡23]

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . .ስብራትን ጠጋኝ፣እሰረኛን አጋዥ፣ድሃን ሀብታም የሚያደርግ፣የተሳሳቾችን ስህተቶች የሚያርምና የሚጠግን፣የኃጢአንን ኃጢአቶች የሚምር፣የሚሰቃዩትን ከስቃይ የሚገላግል፣የደጋግ ትጉሃን አፍቃሪዎቹን ልብ የሚጠግን።

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . . ከሁሉም የሁሉ በላይ የሆነ የላቀ የልዕልና ባለቤት፣ርኅሩህ፣የተሰበሩ ልቦችን፣አቅም የለሽ ደካሞችን፣ወደርሱ የተጠጉትንና በርሱ የተከለሉትን የሚጠግን የሚል ትርጉም አለው።

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . .ልዕልናው ምሉእ የሆነ፣ለነገሮች ሁሉ የተዘረጋ ጸጋው የገዘፈ።

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . .ሁሉም ነገር የተንበረከከለት፣ ሁሉም ነገር የተገዛለት፣አንዱ ነገር ከሌላው ነገር ያላወከው።

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . .የኃያልነት ባለቤት፣የንግሥና፣የግዛት፣የልዕልና፣የዝና እና የአሸናፊነት ባለቤት።

‹‹ኃያሉ ጠጋኙ›› . .ኃያላን የተንበረከኩለት፣ኃይለኞች ድል የተመቱለት፣ነገሥታትና ታላላቆች የተዋረዱለት፣ግፈኞችና እብሪተኞች የተሰባበሩለትና በርሱ የተደመሰሱ ኃያሉ ጠጋኝ ጌታ።

‹‹እርሱ ኃያሉ ጠጋኙ አላህ ነው›› . .

ውበቱ አላህ . .

እርሱ ውበቱ አላህ ﷻ ነው።

አላህ ሆይ! ወደ ተቀደሰው ፊትህ የመመልከትን ለዛ እና ከአንተ ጋር ለመገናኘት መጓጓትንም እንለምነሃለን።

‹‹ውበቱ›› . . እጅግ የተዋቡ ስሞችና እጅግ ምሉእ የሆኑ ባሕርያት ያሉት።

‹‹ውበቱ›› . . የተሟሉ ስሞች ውበት፣የተሟሉ ባሕርያት ውበት እና የፍጹማዊ ምሉእነት ውበት። ‹‹የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን፣ተፈጸመች፤›› [አልአንዓም፡115]

የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረ።

‹‹ውበቱ›› . . የፍጥረተ ዓለም ውበት የርሱን ውበትና ግርማ ሞገሱን ያመለክታል። የርሱ ውበት አእምሮ የማያዳርሰው፣አኳኋኑ ከግንዛቤ በላይ የሆነ ነው። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ . . ያንተን ውዳሴ እኔ ቆጥሬ አልዘልቀውም፤አንተው ራስህ ራስህን እንዳወደስከው ነህ።›› (በሙስሊም የተዘገበ)

‹‹ውበቱ›› . . የቅርጽ ውበትንና የስነምግባር ወበትን የሰጠ፣ከርሱ መልካሙን የመጠበቅ ውበትንም የቸረ።

ውብ ነገር የምትወድ የሆንከው አንተ ውቡ ሆይ! ልቦቻችንን በኢማን አስዋብልን፤ለስነምግባራችንም ውበትን አልብስልን፣ውስጣችንና ውጭያችንንም ውብ አድርግልን።

‹‹እርሱ ውበት ሰጪው አላህ ነው›› . .

ዐዋቂው፣ውስጠ ዐዋቂው፣በዕውቀት ከባቢው አላህ. .

እርሱ በጣም ዐዋቂው፣ውስጠ ዐዋቂው፣በዕውቀት ከባቢው አላህ ነው . .

‹‹በጣም ዐዋቂው፣ውስጠ ዐዋቂው፣በዕውቀት ከባቢው›› . . ዕውቀቱ ግልጹንና ስውሩን፣በምስጢር የሚነገረውንና በይፋ የሚነገረውንም፣ግዴታዎችን፣ሊሆኑ የማይችሉትንና ሊሆኑ የሚችሉትንም ሁሉ፣የላይኛውን ዓለምና የታችኛውንም ዓለም፣ያለፈውን የአሁኑን እና መጪውንም ሁሉ ያካበበ፣ምንም ነገር ከርሱ የማይሰወር።

‹‹በጣም ዐዋቂው፣ውስጠ ዐዋቂው›› ‹‹አላህ የሰዓቲቱ ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፤ዝናምንም ያወርዳል፤በማሕፀኖችም ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃል፤ማንኛይቱ ነፍስም፣በየትኛው ምድር እንደምትሞት አታውቅም፤አላህ ዐዋቂ፣ውስጠ ዐዋቂ ነው።›› [ሉቅማን፡34]

‹‹ዐዋቂው፣በዕውቀት ከባቢው አላህ›› ‹‹በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል፤የምትደብቁትንም፣የምትገልጡትንምያውቃል፤አላህም በልቦች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው።››[አልተጋቡን፡4]

እርሱ ነገሩን ሁሉ በዕውቀት ያካበበ ነው . . ‹‹አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፤ ከምድርም መሰላቸውን፣(ፈጥሯል)፤በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል፤አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አላህም በነገሩ ሁሉ በዕውቀት ያካበበ መኾኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ)።›› [አልጦላቅ፡12]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል ፦ ‹‹አላህም በነገሩ ሁሉ በዕውቀት ያካበበ መኾኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ)።›› [አልጦላቅ፡12]

እርሱ በጣም ዐዋቂው፣ውስጠ ዐዋቂው፣በዕውቀት ከባቢው አላህ ነው . .

በጣም ቅርቡ አላህ . .

እርሱ በጣም ቅርብ የሆነው አላህ ነው . .

ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ የሆንከው ሆይ! . . ተስፋውን ለጣለበት ሁሉ ቅርብ የሆንከው ሆይ!

ለለመነው ሁሉ ቅርብ የሆንከው ሆይ! . . ከደም ስራችን ይበልጥ ለኛ ቅርብ የሆንከው ሆይ!

በአንተና በቃልህ መጽናናትን አድለን . . ‹‹ባሮቼም ከኔ በጠየቁህ ጊዜ፣(እንዲህ በላቸው)፦ እኔ ቅርብ ነኝ፤›› [አልበቀራህ፡186]

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . በልዕልናው ልቆ በዕውቀቱና በተመልካችነቱ ቅርብ ነው።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . ለለመነው ይሰጣል፤ይራራል፤ችግርን ያስወግዳል፣ለጨነቀውና ለጠበበው ሰው ምላሽ ይሰጣል።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . በዕውቀቱ፣በውስጠ ዐዋቂነቱ፣በተቆጣጣሪነቱ፣በእይታውና ሁሉን ከባቢ በሆነው መረጃው ለእያንዳንዱ ፍጡር በጣም የቀረበ።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . ተጸጽቶ ወደርሱ ለተመለሰና በርሱ ለተንጠለጠለ በጣም ቅርብ ነው። ኃጢአትን ይምራል፣ ተውበትን ይቀበላል።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . ባሪያው ወደርሱ ይዞ የቀረበውን ይቀበላል፤ባሪያው ከርሱ ባለው ቅርበት ልክ ወደ ባሪያው ይቀርባል።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . የባሮቹን ሁኔታ ከማንም ይበልጥ በቅርበት የሚያውቅ፣በዕውቀቱና በከባቢነቱ በጣም የቀረባቸው፣ምንም ነገር ከርሱ የማይሰወር።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . በእዝነተ ረቂቅነቱ፣በጥበቃው፣በእርዳታውና በእገዛው ቅርብ የሆነ፣ቅርበቱ በተለይ ለትጉሃን ወዳጆቹ ልዩ የሆነ።

‹‹በጣም ቅርቡ›› . . ባሮቹ መመለሻቸውን ወደርሱ የሚያደርጉ በጣም ቅርብ። ‹‹ከናንተ ይልቅ ወደርሱ የቀረብን ነን።›› [አልዋቂዓህ፡85]

‹‹ቅርቡ›› . . ነፍስ በርሱ ቅርበት የምትጽናና፣በርሱ ውዳሴም የምትርገፈገፍ።

‹‹እርሱ ቅርቡ አላህ ነው . .

ልመናን ተቀባዩ አላህ . . .

እርሱ ልመናን ተቀባዩ አላህ ነው . . . ‹‹ጌታዬ ቅርብ፣(ለለመነው) ተቀባይ ነውና›› [ሁድ፡61]

‹‹ልመናን ተቀባዩ›› . . የባሮቹን ልመና እና ተማጽኖ እርሱ በደነገገላቸው መሰረት ሲለምኑትና ሲጠሩት ይቀበላቸዋል። እንዲጠሩትና እንዲለምኑት ያዘዘውና ምላሽ ለመስጠት ቃል የገባው እርሱ ነውና።

‹‹ልመናን ተቀባዩ›› . . እስረኛው እስር ቤት ሆኖ፣የሰጠመው ባህር ውስጥ ሆኖ፣ደሃው ድህነቱ ውስጥ ሆኖ፣ወላጅ አልባው ህጻን በወላጅ አልባነቱ፣በሽተኛው በሕመሙ ውስጥ ሆኖ፣ልጅ ያጣው መካን በመካንነቱ እርሱን ይማጸናል። እርሱም ይሰጣል፣ይሰማል፣ይቀበላል፣ይፈውሳልም።

‹‹ልመናን ተቀባዩ›› . . የጨነቀውን ሰው ልመና የሚቀበል . . ‹‹ወይም ያ ችግረኛን በለመነው ጊዜ የሚቀበል፣መከራንም የሚያስወግድ፣›› [አልነምል፡62]

ዱዓእ ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው በስሞቹና በባሕርያቱ ሲማጸኑትና ሲለምኑት ነው። እስር ቤት ሆነው የተማጸኑት ብዙዎች ተፈተዋል፤ባሕር ውስጥ ሰጥመው ወደርሱ የወተወቱ ብዙዎች ድነዋል። ብዙ ድሆች ለምነውት ሲሳይ ሰፍቶላቸዋል። ብዙ የቲሞችንም ተንከባካቢና ደጋፊ ሆኖ አሳድጓቸዋል። የመዳን ተስፋቸው የመነመነ ብዙ ሕመምተኞችንም ፈውሷል። ልጅ ያጡ ብዙ መካኖችም እርሱን ተማጽነው ልጅ አግኝተዋል።

እርሱ ልመናን ተቀባዩ አላህ ነው . .

አብሪው አላህ . .

እርሱ አብሪው አላህ ነው . . ‹‹አላህ የሰማያትና የምድር አብሪ [ኑር] ነው፤›› [አልኑር፡35]

‹‹አብሪው›› . . እርሱን ያወቁ ባሮቹን ልብ በኢማን ብርሃን፣ውስጣቸውን በቅን መመሪያ ያበራ።

‹‹አብሪው›› . . በብርሃኑ ጨለማዎችን አስወገደ፤ሰማያትንና ምድርን አበራ፤ወደርሱ የሚጓዙትን ትጉሃን ባሮቹን ልቦና እና መንገዳቸውን አበራ። አላህ አብሪ ነው፤መጋረጃው ብርሃን ነው፤መጋረጃው ቢገለጥ በፊቱ ብርሃን የፍጥረታት እይታ በተቃጠለ ነበር።

እርሱ አብሪው አላህ ነው . .

ጥበበኛው አላህ . .

እርሱ ጥበበኛው አላህ ነው . . ‹‹አላህ ከፈራጆች ሁሉ ይበልጥ ፈራጅ አይደለምን?›› [አልቲን፡8]

‹‹ጥበበኛው›› ነገሮችን በተገቢ መንገዳቸው አሳምሮ የሚያቀናብር፣በዕውቀቱና በውሳኔው መሰረት በተገቢ ቦታቸው የሚያኖር።

‹‹ጥበበኛው›› ሸሪዓዎችን ለጥበባዊ ዓለማ የደነገገ፤ሕግጋትን ለጥበባዊ ዓለማ ያኖረ። ድንጋጌው በዓላማው፣በምስጢራቱ፣በዱንያዊና ኣኽራዊ ግቦቹ ፍጹማዊ ጥበብን ያዘለ ነው።

‹‹ጥበበኛው›› . . በፍጥረታቱና በትእዛዛቱ ውስጥ ጥበቡ የመጠቀ፣ምንም ነገር በከንቱ የማይፈጥር፣ሕጎቹን በከንቱ የማይደነግግ፣በዱንያም ሆነ በኣኽራ ፍርዱ የርሱ ብቻ የሆነ።

‹‹ጥበበኛው›› በውሳኔውና በብያኔው ጥበበኛ፣ድሃውን ድሃ በማድረግ ወይም አንድን ሰው በሽተኛና ደካማ በማድረግ ውሳኔው ጥበበኛ የሆነ፣ቅንብሩ እንከን የሌለበት፣ቃሎቹም ሆኑ ተግባራቱ ጉድለትም ሆነ ዝንፈት የሌለበት፣እርሱ ﷻ የረቀቀና የላቀ ጥበብ ባለቤት ነው።

‹‹ጥበበኛው›› ለባሮቹ ጥበብና ዕውቀትን፣አመዛዛኝነትንና መረጋጋትን፣ነገሮችን በተገቢና ትክክለኛ ቦታቸው የማኖር ብቃትን የሰጠ ጥበበኛ። አላህ ከጥበበኞች ሁሉ በላይ ጥበበኛ ነው። በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ከርሱ ፈቃድ ውጭ ምንም ነገር አይከሰትም። ሐላልና ሐራም አድራጊ እርሱ ብቻ ነው። ሕግ እርሱ የደነገገው ነው፤ሃይማኖት እርሱ ያዘዘውና እርሱ የከለከለው ነው። የርሱን ፍርድ የሚቀለብስ፣ውሳኔውን የሚሽር ማንም የለም።

‹‹ጥበበኛው›› ማንንም አይበድልም . . ባዘዘው በከለከለውና በተናገረው ሁሉ ፍትሐዊ ነው።

እርሱ ፈራጁ ጥበበኛው አላህ ነው . .

አላህ ንጉሡ ነጋሢው እውነተኛው ገዥ

እርሱ ንጉሡ አላህ ነው . . ‹‹ንጉሡ፤ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣›› [አልሐሽር፡23]

‹‹ንጉሡ ነጋሢው›› . . ንግሥና ሁሉ የርሱ የሆነ፣ኃያልነት፣ኩሩነት፣አስገዳጅነት፣አንበርካኪነትና የበላይ አቀነባባሪነት በሆኑ፣በእውነተኛ ንጉሥነት ባሕርያት የሚገለጽ ብቸናው ንጉሥ፣በመፍጠርም ሆነ በትእዛዛቱ ፍጹማዊ ሥልጣን ያለው፣በሰማያትና በምድር ያሉት ሁሉ ባሮቹና ተገዥዎቹ ለመሆን የሚገደዱ።

‹‹ንጉሡ›› . . የኃያልነትና የኩራት ባለቤት፣የባሮቹን ጉዳዮች የሚያስተናብርና የሚያቀናብር፣እነርሱ ተገዳጅ ተገዥዎቹና ታዛዦቹ ሲሆኑ እርሱ ጌታቸውና ፍጹማዊ ባለቤታቸው የሆነ።

ማንኛውም ንጉሥና መሪ የርሱ ባሮችና አገልጋዮች የሆኑ የፍጹማዊ ንግሥና ባለቤት፣በሰማያትም ሆነ በምድር ያለው ትሩፋት ሁሉ የርሱ በረከትና የርሱ ጸጋ ብቻ የሆነ። ‹‹በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፤›› [አልበቀራህ፡225]

‹‹ንጉሡ›› . . ያለ ገደብ የሚሰጥ፤ባሮቹን በስጦታው የሚያጥለቀልቅ፣ልገሳና ችሮታው ከርሱ ምንም የማይቀንስ፣አንዱ ጉዳይ ከሌላው ጉዳይ የማያውከው። ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን፦ ‹‹ . . ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁም ሆኑ ጅኖቻችሁ፣ከመካከላችሁ እጅግ የከፋ ልብ ካለው በኩል ብትተባበሩ ከግዛቴ ቅንጣት አትቀንሱም፡፡ አገልጋዮቼ ሆይ! ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁና ጅኖቻችሁ፣በአንድ አደባባይና ሥፍራ ሆነው ቢለምኑኝና ለያንዳንዳቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ብሰጥ መርፌ ከውቅያኖስ ብትገባ የምታጎድለውን ያህል እንኳ እኔ ዘንድ ካለው ላይ አይጎድልብኝም . . ›› (በሙስሊም የተዘገበ)

‹‹ንጉሡ›› . . ንግሥናን ለሚሻው ይሰጣል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹(ሙሐመድ ሆይ!) በል ፦ የንግሥና ባለቤት የኾንክ አላህ ሆይ! ለምትሻው ሰው ንግሥናን ትሰጣለህ፤ከምትሻውም ሰው ንግሥናን ትገፍፋለህ፤የምትሻውንም ሰው ታልቃለህ፤የምትሻውንም ሰው ታዋርዳለህ። መልካም ነገር ሁሉ በእጅህ ነው፤አንተ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነህና።›› [ኣል ዒምራን፡26]

‹‹ንጉሡ›› . . የፍጥረታቱ ባለቤት፣በዱንያም በኣኽራም እንዳሻው የማድረግና የማዘዝ መብት ያለው። ስለዚህም እርሱን ይከጅሉ፤እርሱን ይማጸኑ፤በዱዓእ፣በልመና እና በውትወታ እርሱ ዘንድ ያለውን ይቀላወጡ።

እርሱ ንጉሡ ነጋሢው እውነተኛው ገዥ አላህ ነው . .

ከጉድለት ሁሉ የጠራው አላህ . .

እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው አላህ ነው . .

በልዕልናው የተቀደሰ፣ውዳሴው የላቀ፣ጸጋዎቹ የገዘፉ . . ‹‹እርሱ አላህ ነው፤ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ንጉሡ፤ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣የሠላም ባለቤቱ፣ . . ነው።›› [አልሐሽር፡23]

የመላእክትና የአልሩሕ ጌታ የሆነው ጥራትና ቅድስና ተገባው . . ከጉድለት ሁሉ የጠራው እውነተኛው ንጉሥ ላቀ።

‹‹እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው አላህ ነው›› . . ከእንከንና ከማንኛውም ጉድለት፣ለርሱ ቅድስና ተገቢ ካልሆነ ማንኛውም ባሕርይ የጠራ።

‹‹እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው ነው›› . . በምሉእነት፣በውበትና በግርማ ሞገስ ባሕርያት የሚገለጽ፤ከነውርና ከጉድለት ሁሉ የጠራ፤እርሱን የሚመስል ምንም ነገር የሌለ፣አቻም ሆነ አንድም ብጤ የሌለው፣ከርሱ ምሉእነት በላይ ምሉእነት የሌለ፣ማንምና ምንም ከስሞቹና ከባሕርያቱ ዲካ የማይደርስ።

‹‹እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው ነው›› . . ልቦች ያጠሩት፣ተስፋዎች ሁሉ በርሱ ላይ የተንጠለጠሉ፣አንደበቶች በምስጋና ያጠሩትና ዘውትር የሚያወድሱት።

‹‹ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣የሠላም ባለቤቱ›› . . ከጉድለት ባሕርያት ሁሉ የጠራው ኃያል፣ከፍጥረታቱ ከአንድም ጋር ከመመሳሰል የላቀ፣ከነውር ሁሉ ፍጹም የጠራ፣በምሉእነቱ ማንምና ምንም እርሱን ከመምሰል ፈጽሞ የራቀ።

‹‹እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው ነው›› . . የበረከትና የጸጋዎች፣የትሩፋትና የውዳሴ ባለቤት የሆነ፣በረከቶች ከርሱ ወደርሱ የሆኑ፣ባሮቹን የሚባርክ በረከት፣የሻውን ጸጋና በረከት በማፍሰስ የሚባርካቸው።

እርሱ ከጉድለት ሁሉ የጠራው አላህ ነው . .

የሠላም ባለቤቱ አላህ . .

እርሱ የሠላም ባለቤቱ አላህ ነው . .

አላህ ﷻ ሰላም ነው፤የሰላም ምንጭም እርሱ ነው። እርሱ ሰላም ካልሰጠውና ካላዳነው ማንም ባሪያ አይድንም። እርሱ ካላመቻቸለትም ስኬትን አያገኝም።

እርሱ የሠላም ባለቤት ነው . .ከማንኛውም እንከንና ጉድለት ነጻ የሆነ፤ከርሱ በቀር ያለው ሁሉ ለእንከን ለጉድለትና ለነውር ተጋላጭ መሆን የሚችል።

እርሱ የሠላም ባለቤት ነው . . ባሕርያቱ ከፍጥረታቱ ባሕርያት ጋር ከመመሳሰል ነጻ የሆኑ፣ከጉድለትና ከእንከን ሁሉ የራቁ፣ዕውቀቱ ምሉእና ነጻ የሆነ፣ፍትሑ አጠቃላይና ተደራሽ የሆነ፣ግዛቱ ከጉድለትና ከእንከን የነጻ ምሉእ የሆነ፣ፍርዱ ፍትሐዊና ነጻ የሆነ፣ሥራው የነጻና ሰላም የሆነ፣እርሱም ሰላም የሰላም ምንጭም እርሱ የሆነ፤የግርማ ሞገስና የክብር ባለቤት የሆነ ጌታ ላቀ።

አላህ ﷻ በዱንያም በኣኽራም ለባሮቹ ሰላምን ዘርግቶላቸዋል። ‹‹ሰላም በኢብራሂም ላይ ይኹን።›› [አልሷፍፋት፡109] , ‹‹ሰላም በሙሳና በሃሩን ላይ ይኹን።›› [አልሷፍፋት፡120] , ‹‹በመልክተኞቹም ላይ ሰላም ይኹን።›› [አልሷፍፋት፡181]

ኣኽራን በተመለከተ አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ጸጥተኞች ኾናችሁ በሰላም ግቧት፣(ይባላሉ)።›› [አልሒጅር፡46]

የሠላም ባለቤት . . እርሱ ምንም ፍርሃት የማይኖርበት የሰላም ባለቤት ነው፤ምንም ስጋት የማይከተለው ምሕረትም ነው። እርሱ የሰላም ባለቤት ነው፣ሰላምም ከርሱ ነው።

እርሱ የሰላም ባለቤቱ አላህ ነው . .

እውነቱ አላህ . .

እርሱ እውነቱ አላህ ነው . . ‹‹ይህ፣አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፤ . . በመኾኑ ነው።›› [አልሐጅ፡6]

‹‹እውነቱ አላህ›› . . በእርሱነቱና በባሕርያቱ እውነት፣ባሕርያቱ የተሟሉ፣መኖሩና ሕልውናው ከራሱ እርሱነት የመነጨ፣በርሱ ቢሆን እንጂ ማንኛውም ነገር ሕልውና የሌለው፣በግርማ ሞገስ በውበትና በፍጹማዊ ምሉእነት ሲገለጽ የኖረ ያለና የሚኖር፣በደግነትና በችሮታው ሲታወቅና እንደታወቀ የኖረና የሚኖር።

‹‹እውነቱ አላህ›› . . ቃሉ እውነት፣ተግባሩ እውነት፣ከርሱ ጋር መገናኘትም እውነት፣መጽሐፎቹም እውነት፣ሃይማኖቱም እውነት፣እርሱን ብቻ ያለ ምንም ተጋሪ ማምለክም እውነት፣ከርሱ ጋር ተያያዥነት ያለው ነገር ሁሉ እውነት የሆነ እውነቱ አላህ። ‹‹ይህ፣አላህ እርሱ እውነት በመኾኑ፣ከርሱም ሌላ የሚገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሸት በመኾኑ፣አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመኾኑ ነው።›› [አልሐጅ፡62]

እርሱ እውነቱ አላህ ነው . .

ጸጥታን ሰጪው ባሮቹን ጠባቂው አላህ . .

እርሱ ጸጥታን ሰጪው ባሮቹን ጠባቂው አላህ ነው . . ‹‹እርሱ አላህ ነው፤ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ንጉሡ፤ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣የሠላም ባለቤቱ፣ጸጥታን ሰጪው፣ባሮቹን ጠባቂው፣. . ነው።›› [አልሐሽር፡23]

‹‹ጸጥታን ሰጪው›› . . በባሮቹ መካከል ጸጥታን፣በፍጥረታቱ ዘንድ ደህንነትን፣በመለኮታዊ ራእዩ እርካታን የሚያሰራጭ። ‹‹ከፍርሃትም ያረካቸውን [ጸጥታ የሰጣቸውን]፣›› [ቁረይሽ፡4]

‹‹ጸጥታን ሰጪው›› . . ምሉእ በሆኑ ባሕርያት፣በግርማ ሞገሱና በውበቱ ራሱን ያወደሰ፣መልእክተኞቹን ልኮ መጽሐፎቹን በታአምራትና በማስረጃዎች ያስተላለፈ፣የመልክተኞቹን መልክት እውነተኛነት በተአምርና በማስረጃ ያረጋገጠ።

‹‹ጸጥታን ሰጪው›› . . ታማኙ፣የፍጥረታቱ የበላይ ጠባቂ፣ተቆጣጣሪና ተመልካች የሆነ።

‹‹ጸጥታን ሰጪው›› . . ምንዳና ሽልማትን የማይቀንስ፣ቅጣትን የማይጨምር፣ለትሩፋትና ችሮታውን ለመለገስ፣ለደግነትና ለቸርነት ከማንም በላይ ተገቢ የሆነ።

‹‹ባሮቹን ጠባቂው›› . . የተሰወሩ ነገሮችንና ልቦች የደበቁትን የሚያውቅ፣ነገሮችን ሁሉ በዕውቀቱ ያካበበ።

‹‹ባሮቹን ጠባቂው›› . . ባሮቹን በበላይነት የተቆጣጠረ፣አንበርክኳቸው በሥልጣኑ ስር ያደረገ፣የተንከባከባቸውና ድርጊቶቻቸውንና ሁኔታዎቻቸውን ያወቀ፣በዕውቀቱ ያካበባቸው፣ማንኛውም ነገር ለርሱ ገርና ቀላል የሆነ፣ለማንኛውም ነገር አስፈላጊው የሆነ። ‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።›› [አልሹራ፡11]

እርሱ ጸጥታን ሰጪው፣ባሮቹን ጠባቂው አላህ ነው።

ይቅር ባይ ምሕረተ ብዙው፣አብዝቶ የሚምር አላህ . .

እርሱ ይቅር ባይ መሓሪ፣አብዝቶ የሚምር አላህ ነው . . ‹‹አላህ ይቅር ባይ መሓሪ ነውና፤›› [አልሐጅ፡60]

ይቅር ባይ፣ምሕረተ ብዙው፣አብዝቶ የሚምር አላህ . . ሁሌም በመሐሪነቱ የሚታወቀው፤ለባሮቹ ይቅርባይና ምሕረት ሰጭ በመሆን የሚገለጸው፤እያንዳንዱ ሰው የርሱን ይቅርታና ምሕረት፣እንደዚሁም እዝነቱንና ችሮታውን ለመፈለግ የሚገደደው ምሕረተ ብዙው አላህ።

አንተ መስፈርቱን አሟልቶ ለጠየቀህ ሁሉ ይቅርታ ለመለገስና ምሕረት ለመስጠት ቃል የገባኸው ጌታ ሆይ! ይቅር በለን። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹እኔም ለተጸጸተ፣ለአመነም፣መልካምንም ለሠራ፣ከዚያም ለተመራ ሰው በእርግጥ መሓሪ ነኝ።›› [ጣሃ፡82]

አንተ ምሕረተ ብዙው ሆይ! እርግፍ አድርገን በመተው ከኃጢአቶቻችን የምንመለስበትን ልባዊ ጸጸት እንለምነሃለን። በፈጸምናቸው ጥፋቶችና ጥሰቶች ተጸጽተን ለትእዛዞችህ ተገዥ ለመሆን አድለን፤አንተ በጣም መሐሪው ነህና ማረን።

አላህ ሆይ! ምሕረትን የምትወድ ነህና ይቅር በለን . . በጣም መሐሪ በጣም አዛኝ መሆንህን ነግረህናልና ማረን . . ‹‹ባሮቼን፣እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው።›› [አልሒጅር፡49] አንተ በጣም መሐሪ የሆንክ ጌታ ሆይ! ማረን።

እርሱ ይቅር ባይ መሓሪ፣አብዝቶ የሚምር አላህ ነው . .

ጸጸትን ተቀባዩ አላህ . .

እርሱ ጸጸትን ተቀባዩ አላህ ነው . . ‹‹አላህ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና።›› [አልተውባህ፡118]

‹‹ጸጸትን ተቀባይ›› . . በችሮታውና በደግነቱ ለባሮቹ ተጸጽቶ መመለስን (ተውበትን) የደነገገ፣ከዚህም አልፎ ክፉ ሥራን ወደ በጎ ሥራነት ለመቀየር ቃል የገባላቸው።

‹‹ጸጸትን ተቀባይ›› . . ባሮቹን በተውበታቸው ላይ እንዲጸኑ የሚያደርግ፣ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድም የሚያግዛቸው።

‹‹ጸጸትን ተቀባይ›› . . በጥፋታቸው የሚጸጸቱ ሰዎችን ጸጸት የሚቀበል፤የኃጢአንን ኃጢአት የሚምር። ኃጢአትን እርግፍ አድርጎ በመተው ከልቡ ተጸጽቶ የተመለሰን ሰው ጸጸት አላህ ይቀበላል። ከልብ ወደርሱ መመለስንና ተውበትን ለነርሱ በመግራት፣ከዚያም ተውበታቸውን ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ ኃጢአቶቻቸውን በማበስ ጸጸትን ተቀባይ ነው።

‹‹ጸጸትን ተቀባይ›› . . ለባሮቹ ተውበት ማድረግን የገራላቸው፣በተውበት ላይ የሚያበረታታቸው፣በመሐሪነቱ የሚወዳጃቸው።

‹‹ጸጸትን ተቀባይ›› . . ከባሮቹ ጸጸትን የሚቀበል። በዚያ ላይ የሚያጸናቸው። ደረጃዎችን ከፍ የሚያደርግ።ኃጢአቶችን የሚያብስ ጌታ ግርማ ሞገሱ ላቀ።

እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አላህ ነው . .

አንዱ ብቸኛው አላህ . .

እርሱ አንዱ ብቸኛው አላህ ነው . .

በአንተነትህ አንድ የሆንከው፣በስሞችህም አንድ የሆንከው፣በባሕርያትህም አንድ የሆንከው አላህ ሆይ!

የልቦና ፍጹምነትን፣ፍቅርህንና የተስፋ ቃልህን ትለግሰን ዘንድ እንለምንሃለን . . አንተ ብቸኛው፣የሁሉ መጠጊያ የሆንከው ሆይ!

‹‹ብቸኛው›› . . በእርሱነቱ (በዛቱ)፣በስሞቹና በባሕርያቱ አንድና ብቸኛው የሆነ፤አቻ አምሳያም ሆነ ተነጻጻሪ የሌለው። ‹‹ለርሱ ሞክሼን ታውቃለህን?››[መርየም፡65]

‹‹ብቸኛው›› . . አምልኮት በሚገባው አምላክነቱ አንድ ብቻ የሆነ፤ከርሱ በቀር በእውነት የሚመለከ ሌላ አምላክ የሌለ፤ይብዛም ይነስ ከዕባዳ ለርሱ ብቻ እንጂ ምንም ነገር ለማንምና ለምንም የማይዞር።

‹‹አንዱ ብቸኛው›› . . በሁሉም ምሉእ ባሕርያቱ አንድ የሆነ፣በዚህ ምንም ሸሪክና ተጋሪ የሌለው። ባሮቹ በእሳቤ በአንደበትና በተግባር ለፍጹማዊ ምሉእነቱና ለአንድ ብቸኛ አምላክነቱ ዕውቅና በመስጠት እርሱን ብቻ የሚግገዙት።

‹‹ብቸኛው›› . . የፍጥረታት ሁሉ ብቸኛው ግብ፣ብቸኛው ተመላኪ ጌታ፣ልቦች ይህንኑ በፍጹምነት የሚመሰክሩለት፣እይታዎች የሚንጠለጠሉበት።

‹‹አንዱ ብቸኛው›› . . አላህ ﷻ ባሮቹን አንድነቱንና ምንም ሸሪክ የሌለው አምላክ የመሆኑን እምነት የተፈጥሯቸው አካል ያደረገ፣እርሱን ትቶ ፊቱን በአምልኮ ወደ ሌላ ያዞረ ተሳክቶለት፣ከርሱ በቀር ሌላ ያመለከ ታድሎ የማያውቅ፣ሌላን ከርሱ ጋር ያጋራ ሁሉ ፍጻሜው ውድቀት ብቻ የሆነ።

እርሱ አንዱ ብቸኛው አላህ ነው።

አላህ የሁሉ መጠጊያ ነው . .

እርሱ የሁሉ መጠጊያ አላህ ነው . . ‹‹በል፦ እርሱ አላህ አንድ ነው። (አላህ) የሁሉ መጠጊያ ነው።›› [አልኢኽላስ፡1-2]

‹‹የሁሉ መጠጊያ›› . . በስሞቹና በባሕርያቱ ምሉእ የሆነ፣ጉድለትም ሆነ እንከን የማይደርስበትና የሌለበት።

‹‹የሁሉ መጠጊያ›› . . ፍጥረታት ሁሉ ከርሱ የሚፈልጉ እርሱ ግን ከማንም ምንም የማይፈልግ፣በራሱ ብቻ የተብቃቃ። ‹‹የሚመግብ፣የማይመገብም ሲኾን፣››[አልአንዓም፡14]

‹‹የሁሉ መጠጊያ›› . . በእርሱነቱ በስሞቹ በባሕርያቱና በተግባራቱ ፍጹማዊ ምሉእነት ያለው በመሆኑ፣ፍጥረታት ሁሉ ለሁሉም ፍላጎቶቻቸውና ለችግሮቻቸው የርሱን ረድኤትና እገዛ የሚጠብቁ።

‹‹የሁሉ መጠጊያ›› . . አቀናባሪ ጌታ፣ያሻውን የሚፈጽም ፍጹማዊ ባለቤት።

‹‹የሁሉ መጠጊያ›› . . ልቦች ሁሉ ለጉዳዮቻቸውና ለችግሮቻቸው እርሱን ሲማጸኑ የሚሰጣቸውና የማይከለክላቸው። ሲለምኑት የሚሰማቸውና ችግራቸውን የሚያስወግድላቸው። ከርሱ የራቁት ሲጠሩት ሰምቷቸው ግንኙነቱን መላልሶ የሚቀጥልላቸው። የፈሩትንና የተሸበሩትን የሚያረጋጋና የሚያጽናና። በርሱ ላይ ተስፋ የጣሉትን ከግባቸው የሚያደርስ። አደጋ የተጋረጠባቸውን ነጻ የሚያወጣ። ባሮቹን በአምልኮው ሲተጉ ከፍ የሚያደርጋቸው።

‹‹እርሱ የሁሉ መጠጊያ አላህ ነው . .

አሸናፊው አላህ . .

እርሱ አሸናፊው አላህ ﷻ ነው . . ‹‹አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።›› [አልአንፋል፡67]

አሸናፊው ብርቱውና ድል አድራጊው አላህ።

የኃይለኞችና የብርቱዎች ሁሉ ኃይልና ብርታት የማይጎዳው፤ምንም የማይሳነው . . የኃያላን ሁሉ ድል አድራጊ ኃያል የሆነው አላህ ﷻ ላቀ።

‹‹አሸናፊው›› . . ፍጹማዊ አሸናፊት የርሱ ብቻ የሆነ፤ፍጥረታት ሁሉ ለርሱ የሚዋደቁለትና የሚንበረከኩለት፣ኃይለኛ ሁሉ እርሱ ፊት ተዋራጅ የሆነ።

‹‹አሸናፊው›› . . የኃይል አሸናፊነት፣የድል አድራጊነት አሸናፊነት፣የአይበገሬነት አሸናፊነት፣ሁሉም አሸናፊነት የርሱ ብቻ የሆነ። ፍጥረታት ሁሉ ፈጽሞ ሊጎዱት የማይችሉ፣ሁሉንም ያንበረከከ፣ሁሉም ለኃያልነቱ የተዋረደለት።

‹‹አሸናፊው›› . . አሸናፊነትን እርሱ ለሚሻው ሰው የሚሰጥ፣ከሻው ሰውም የሚነጥቅ፣ያሻውን ሰው የሚያዋርድና በጎው ሁሉ በርሱ እጅ የሆነ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ኃይል ሁሉ በሙሉ፣የአላህ ብቻ ነውና፤›› [ዩኑስ፡65]

በርሱና ከርሱ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በዘር፣በማእረግ፣በሀብትም ሆነ በሌላ ምክንያት አሸናፊነት አይኖርም።

‹‹አሸናፊው›› . . ማንም ሰው ከርሱ በኩል ከሚሰጠው ውጭ አሸናፊነትን፣በርሱ ችሮታ እንጅ ኃይልን የማያገኝ። መጠበቅ የፈለገ ጥበቃን ከአላህ ይፈልግ፤አሸናፊነትን የሻ ሰውም ልቦናውን ወደ አላህ ይመልስ። ‹‹አሸናፊነትም ለአላህ፣ለመልክተኛውና ለምእምናን ነው፤›› [አልሙናፊቁን፡8]

እርሱ አሸናፊው አላህ ነው

የበላይ አሸናፊው አላህ . .

እርሱ የበላይ አሸናፊው አላህ ነው . . ሰዎችና አጋነንትን የሚያንበረክክ የበላይ አሸናፊ ፦ ‹‹እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን አሸናፊ ነው፤እርሱም ጥበበኛው፣ውስጠ ዐዋቂው ነው።›› [አልአንዓም፡18]

‹‹የበላይ አሸናፊ›› . . በልዕልናውና በዕውቀቱ ከባቢነት፣በአቀነባሪነቱ፣ስለነርሱ ባለው ዕውቀቱና በኃያልነቱ ፍጥረታቱን አንበርክኳል። በዚህ ገደብ የለሽ ግዙፍ ዩኒቨርስ ውስጥ ከርሱ ፈቃድና ከዕውቀቱ ውጭ የሚሆን ምንም ነገር የለም።

‹‹የበላይ አሸናፊ›› . . እምቢተኞችንና ትእቢተኞችን በታላላቅ ማስረጃዎች ዝም አስኝቶ፣አምላክነት ጌትነት መልካም ስሞችና የመጠቁ ባሕርያት ተገቢው መሆናቸውን ያረጋገጠላቸው የበላይ አሸናፊ።

‹‹አንበርካኪው አሸናፊ›› . . ማንኛውንም ነገር ያንበረከከ የበላይ አሸናፊ፣ፍጥረታት ሁሉ ለኃያልነቱና ለምሉእ ብቃቱ ተዋርደው የተገዙለት።

‹‹የበላይ አሸናፊ›› . . ግፈኞችን፣አምባገነኖችንና እብሪተኞችን አንበርክኮና አንኮታክቶ የሚያዋርድ። ‹‹አንድ አሸናፊ ለኾነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለጹበትን ቀን (አስታውስ)።›› [ኢብራሂም፡48]

‹‹የበላይ አሸናፊ›› . . ፈቃዱና ፍላጎቱ ከፍጥረታቱ መካከል የቱንም ያህል ኃያል ቢሆን ማንም የማያስቀረውና ተፈጸሚነት ያለው። እጹብ ድንቅ የሆነ ሥራውን የፈለገውን ያህል ቢራቀቁ ሊደርሱበት የማይችሉ። ማንም አንደበተ ርቱእ የጥበቡን ምጥቀትና ውበት መግለጽ የሚሳነው የበላይ አሸናፊ።

እርሱ የበላይ አሸናፊው አላህ ነው . .

ሲሳይን ሰጪው አላህ . .

እርሱ ሲሳይን ሰጪው አላህ ነው . . ‹‹አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ፣የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው።›› [አልዛሪያት፡58]

‹‹ሲሳይን ሰጪው›› . . የፍጥረታቱ ሲሳይና ምግባቸው በርሱ እጅ የሆነ። ለሻ ሰው ሲሳይ የሚያሰፋና ባሻው ሰው ላይ የሚያጠብ። ነገሮችን ሁሉ የሚያቀነባብር፣የሰማያትና የምድር ድልብ ሀብት መክፈቻ በእጁ የሆነ ሲሳይ ሰጪ ጌታ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦‹‹በምድርም ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለችም፣ምግቧ በአላህ ላይ ያለ ቢኾን እንጂ፤ማረፊያዋንም፣መርጊያዋንም ያውቃል፤›› [ሁድ፡6]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ከተንቀሳቃሽም ምግቧን ለመሸከም የማትችለው ብዙ ናት፤አላህ ይመግባታል፤እናንተንም፣(ይመግባል)፤እርሱ ሰሚው፣ዐዋቂው ነውና።›› [አልዐንከቡት፡60]

አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ጌታህ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ያጠባልም፤እርሱ በባሮቹ ኹኔታ ውስጠ ዐዋቂ ተመልካች ነውና።›› [አልኢስራእ፡30]

በተጨማሪም አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹አላህም፣ለሚሻው ሰው ያለ ግምት ይሰጣል።›› [አልበቀራህ፡212]

‹‹ሲሳይን ሰጪው›› . . ሰዎች ሁሉ የርሱን እጅና ሲሳይ የሚጠብቁ ድሆች ሲሆኑ፣ታዛዥ ተገዥውንም ሆነ አመጸኛ ኃጢኡን፣ያለፉትን ያሉትንና የሚመጡትን . . ሁሉንም በየፈርጁ የሚመግብ ሲሳይን ሰጪው።

‹‹ሲሳይን ሰጪው›› . . በቅን ልቦና ወደርሱ ለተመለሰው ሰው የተሟላ ሲሳይ የሚሰጥና ጸጋውን የሚዘረጋለት። የለመነውን ሰው በዕውቀትና በኢማን የሚቀልብ። ለጠየቀው ሰው ለልቦና መጥራትና ለሃይማኖታዊ ትጋት አጋዥ የሆነ ሐላል ሲሳይን የሚለግስ።

እርሱ ሲሳይን ሰጪው አላህ ነው . .

እዝነተ ረቂቁ አላህ . .

እርሱ እዝነተ ረቂቁ አላህ ነው . . ‹‹ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው፤›› [ዩሱፍ፡100]

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . ፍጡራንን እርስ በርሳቸው እንዲተዛዘኑ፣ እንዲተሳሰቡና እንዲዋደዱ ያደረገ እዝነተ ረቂቅ ጌታ።

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . ረቂቅ ዕውቀቱ ምስጢራትንና ስውር ነገሮችን ሁሉ ያካበበ። ግልጽና ድብቁን ሁሉ የሚያይ። ለምእመናን ባሮቹ እዝነተ ረቂቅ የሆነ። ባላሰቡትና ባልገመቱት መንገድ በእዝነተ ረቂቅነቱና በቸርነቱ የሚጠቅማቸውን ሁሉ የሚያደርስላቸው።

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . የተትረፈረፈ ስጦታና ችሮታ የሚለግስ ቸር አምላክ።

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . ለባሮቹ ርኅሩህ የሆነ። ‹‹አላህ በባሮቹ ርኅሩህ ነው፤›› [አልሹራ፡19]

ለዛሬው የዱንያ ሕይወትና ለመጪው የኣኽራ ሕይወታቸው ጠቃሚ የሆነውን የሚሰጣቸው፤ለየዱንያና ለኣኽራ ሕይወታቸው ጎጂ የሆነውን ሁሉ የሚከለክላቸው።

እዝነተ ረቂቁ . . ዓይኖች አያዩትም፤እርሱ ግን ዓይኖችን ያያል። ‹‹ዓይኖች አያገኙትም፤(አያዩትም)፤እርሱም ዓይኖችን ያያል፤እርሱም ርኅራኄው፣ረቂቁ፣ውስጠ ዐዋቂው ነው።›› [አልአንዓም፡103]

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . የሁሉንም ነገሮች ድብቅ ምስጢር የሚያውቅ፣ረቂቅ ሥራዎችን ሁሉ የሚቆጣጠር፣ቀንም ሆነ ማታ ምንም ነገር ከርሱ የማይሰወር፣የባሮቹን ጥቅሞች ጥቃቅኑንና ውስብስቡን ሁሉ የሚያውቅና የሚያዝንላቸው።

‹‹እዝነተ ረቂቁ›› . . ነገሮችን ሲወስን ለባሮቹ የሚራራ፣ወሳኔውን ሲያስተላልፍ ረድኤቱን የሚቸራቸው። ችግር ሲጠና እና መከራ ሲበረታ የመፍትሔ በሮችን የሚከፍትላቸው፣ነገሮች ሲወሳሰቡ የሚያገራላቸው።

እርሱ እዝነተ ረቂቁ አላህ ነው . .

በትክክል ፈራጁ አላህ . .

እርሱ በትክክል ፈራጁ አላህ ነው . . ‹‹እርሱም በትክክል ፈራጁ፣ዐዋቂው ነው፤›› [ሰበእ፡26]

‹‹ከፋቹ፣በትክክል ፈራጁ›› . . እዝነቶቹንና በረከቶቹን የሚከፍትልን . . . ‹‹አላህ ለሰዎች ከችሮታ የሚከፍታት ለርሷ ምንም አጋጅ የላትም፤የሚያግደውም ከርሱ በኋላ ለርሱ ምንም ለቃቂ ለውም፤›› [ፋጢር፡2]

‹‹ከፋቹ፣በትክክል ፈራጁ›› . . በረከቶቹን ለኛና ለእናንተም የከፈተልን . . ከጸጋዎቹና ከስጦታዎቹ ያቋደሰን . . ይቅርታውንና ምሕረቱን የጨመረልን።

የተዘጉ ልቦችን በቅን መመሪያና በኢማን ቁልፎች የሚከፍት ከፋቹ አላህ።

‹‹ከፋቹ፣በትክክል ፈራጁ›› . . የእዝነትና የቸርነት በሮቹን በሰፊው የሚከፍት። በባሮቹ ላይ ጸጋና በረከቱን ደግሞ ደጋግሞ የሚያዘንብ። የዕውቀትና የጥበብ ብርሃንን አእምሯቸው ውስጥ የሚያፈነጥቅ። ልቦች በርሱ ያምኑ ዘንድ የቅን መመሪያ በሮቹን የሚከፍትላቸው።

‹‹በትክክል ፈራጁ›› . . በሸሪዓዊ ሕጎቹ፣በብያኔዎቹና በመቀጫዎቹ በባሮቹ መካከል የሚፈርድ። የጻድቃንን ዓይነ ሕሊና በጥበቡ የከፈተ። እርሱን ያውቁት ዘንድ ልቦቻቸውን ለርሱ ፍቅርና ለተውበት የከፈተላቸው፤ጸጋና ቸርነቱን በየዓይነቱ የዘረጋላቸው።

‹‹ከፋቹ፣በትክክል ፈራጁ›› . . የጭንቀትና የውጥረት ደመናን ከባሮቹ ላይ የሚገፍ። እፎይታና እርካታን የሚያስገኝላቸው። ከችግርና ከመከራ የሚያወጣቸው፣ጉዳትን የሚያስወግድ።

‹‹በትክክል ፈራጁ›› . . በመጪው የኣኽራ ሕይወት በባሮቹ መካከል በትክክል የሚፈርድ፣ምስጉኑ ፍትሐዊ አምላክ።

እርሱ በትክክል ፈራጁ አላህ ነው . .

ተብቃቂው አብቃቂው ባለጸጋው አላህ . .

እርሱ ተብቃቂው አብቃቂው ባለጸጋው አላህ ነው . .

‹‹ተብቃቂው ባለጸጋ›› . . በርሱነቱ ከማንም እና ከምንም በራሱ የተብቃቃ። የፍጹማዊ ተብቃቂነትና የምሉእ ጸጋ በባለቤት የሆነ። ባሕርያቱና ምሉእነቱ በምንም መልኩ ፈጽሞ ለጉድለት የማይጋለጥ። ተብቃቂቱና ፍጸጹማዊ ባለጸጋነቱ ከርሱነቱና ከሕልውናው መገለጫዎች አንዱ በመሆኑ ከማንምና ከምንም የተብቃቃ መሆኑ የግድ የሆነ። ፈጣሪ፣ሁሉን ቻይ፣ሲሳይን ሰጭና መጽዋች መሆኑም እንዲሁ የግድ ነው። በምንም መልኩ ከማንም ምንም አይፈልግም። የሰማያትና የምድር፣የዱንያና የኣኽራ ሀብት መጋዝኖች ሁሉ በእጁ የሆነ በራሱ የተብቃቃ ጌታ ነው።

‹‹ተብቃቂው›› . . ከባሮቹ የተብቃቃ፣እንዲመግቡትም ሆነ እንዲያጠጡት የማይፈልግ። ስለ አስፈለጉትና በነርሱ ሥልጣኑንና ኃይሉን ለመጨመር ብሎ ያልፈጠራቸው። በነርሱ ለመጽናናትና ከብቸኝነት ለመውጣት አልሞ ያላስገኛቸው። በተቃራኒው ለምግብና ለመጠጣቸው፣ለሁሉም ጉዳዮቻቸው እነርሱ እርሱን የግድ የሚፈልጉት ተብቃቂ ጌታ ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ጋኔንንና ሰውንም፣ሊግገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም። ከነሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ሊመግቡኝም አልሻም።›› [አልዛሪያት፡56-57]

‹‹አብቃቂው›› . . ሰዎችን ከችግሮቻቸውና ከድህነታቸው የሚያወጣቸው፣በመስጠቱ ሀብቱ ፈጽሞ የማይጎድል፣ባሮቹ ከርሱ በስተቀር ሌላ አስፈላጊያቸው ያልሆነ ተብቃቂ ጌታ። ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን፦ ‹‹ . . ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁም ሆኑ ጅኖቻችሁ፣ከመካከላችሁ እጅግ የከፋ ልብ ካለው በኩል ብትተባበሩ ከግዛቴ ቅንጣት አትቀንሱም። አገልጋዮቼ ሆይ! ከናንተ የቀደሙትም ሆኑ የሚከተሉት፣ሰዎቻችሁና ጅኖቻችሁ፣በአንድ አደባባይና ሥፍራ ሆነው ቢለምኑኝና ለያንዳንዳቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ብሰጥ መርፌ ከውቅያኖስ ብትገባ የምታጎድለውን ያህል እንኳ እኔ ዘንድ ካለው ላይ አይጎድልብኝም . . ›› (በሙስሊም የተዘገበ)

‹‹አብቃቂው›› . . ልቦቻቸውን በቅን መመሪያ በማብራት ባሮቹን የሚያበጅ። እርሱን በማወቅ፣በግርማ ሞገሱ፣በልዕልናው፣በፍቅሩና በውዴታው ባሮቹን በጸጋው በማብቃቃት ከቁሳዊ ጸጋና መብቃቃት የላቀና የመጠቀ መብቃቃትን የሚያጎናጽፋቸው።

መስጠት የማያጎድልብህ ጌታ ሆይ! . . በሐላሉ ነገር ከሐራሙ ሁሉ የምንብቃቃ አድርገን፤አንተ ተብቃቂው አብቃቂው ነህና።

እርሱ ተብቃቂው አብቃቂው አላህ ነው . .

ሁሉን ቻይ አኑዋሪው . .

እርሱ ሁሉን ቻይ አኑዋሪው አላህ ነው . . ‹‹አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ [ቀልቦ የሚያኖር] ነው።›› [አልኒሳእ፡85]

‹‹ሁሉን ቻይ አኑዋሪው›› . . ለፍጥረታቱ ሁሉ ቀለባቸውን የሚያደርስላቸው። የሚያኖራቸውንና የሚኖሩበትን ያመቻቸላቸው። ርሃብና ጥማታቸውን የሚያስወግድላቸው። የተድላ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው። ሁሉን ቻይ አኑዋሪና ቀላቢ አምላክ።

‹‹ሁሉን ቻይ አኑዋሪው›› . . ወደ እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ቀለቡን የሚያደርስ። ለፍጥረታቱ ሲሳይን በመዘርጋት በጥበቡና በሻው መንገድ የሚያዳርሳቸው መጋቢ አምላክ።

‹‹ሁሉን ቻይ አኑዋሪው›› . . ልቦችን በዕውቀትና በጥበብ ዓይነቶች በመቀለብ መንፈስን ሕያው የሚያደርግና ለነፍስ እርካታን የሚያጎናጽፍ።

የፍጥረታትህን ጉዳዮች ሁሉ የምታቀነባብረው፣የዱንያና የኣኽራ ሕይወታቸው አስተናባሪ የሆንከው አላህ ሆይ! . . ጥበቃህን፣ይቅርታህንና ምህሕረትህን እንለምነሃለን። ‹‹አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ [ቀልቦ የሚያኖር] ነው።›› [አልኒሳእ፡85]

እርሱ ሁሉን ቻይ አኑዋሪው አላህ ነው . .

አላህ ተጠባባቂው በቂው . . .

እርሱ ተጠባባቂው በቂው አላህ ነው . .

አላህ በፍጥረታቱ ላይ ተቆጣጣሪ መርማሪ ነው . . ከምንም ነገር በቂያቸው እርሱ ነው . . ‹‹አላህ ባሪያውን በቂ አይደለምን?››[አልዙመር፡36]

‹‹ተጠባባቂው መርማሪው›› . . ባሮቹን በጥልቀት የሚያውቅ፣በርሱ ላይ ለተማመኑትና እርሱን መጠጊያቸው ላደረጉት በቂያቸው የሆነ፣ለባሮቹ በትንሹና በትልቁ ሥራቸው በጥበቡና በዕውቀቱ መሰረት ዋጋቸውን የሚከፍል።

በቂያችን አላህ ነው፣እርሱም እጹብ ድንቁ ወደርየለሽ መጠጊያ ነው . . ሐስቡነልሏሁ ወንዕመል ወኪል . . ነቢዩ ኢብራሂም u ወደ እሳት ሲወረወሩ የደገሙትና እሳቱን ቅዝቃዜና ሰላም ያደረገላቸው፣የታላቁ ሙሐመድ ﷺ ባልደረቦችም ከጠላት ጋር ሲገጥሙ ያሉት ብሂል። ይህንኑ በማስመልከት አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ሰዎች ለናንተ (ጦር) አከማችተዋልና ፍሩዋቸው›› [ኣል ዒምራን፡173]

‹‹በቂው›› . . ለሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ለባሮቹ በቂያቸው የሆነ። በተለይ ደግሞ በርሱ ለአመነና በርሱ ላይ ለተማመነ፣ሃይማኖታዊም ሆኑ ዓለማዊ ጉዳዮቹን ከርሱ ለሚያመነጭ ትጉህ አማኝ በቂው የሆነ ጌታ።

ሲባሉ መልሳቸው እንዲህ ነበር ፦ ‹‹በቂያችንም አላህ ነው፣ምን ያምርም መጠጊያ! ያሉ ናቸው። ከአላህም በኾነ ጸጋና ችሮታ ክፉ ነገር ያልነካቸው ኾነው ተመለሱ፤የአላህንም ውዴታ ተከተሉ፤›› [ኣል ዒምራን፡173-174] ,‹‹እርሱም ከተቆጣጣሪዎች ሁሉ ይበልጥ ፈጣን ነው።›› [አልአንዓም፡62]

‹‹ተጠባባቂው መርማሪው›› . . ባሮቹ የገለጡትንም ሆነ በውስጣቸው የደበቁትንም በዝርዝርና በፍጹምነት የሚያውቅ መርማሪው ጌታ። በቂያችን የሆንከው ጌታ ሆይ! ከሚያሳስበን ነገር አንተ በቂያችን ሁን፤ወደ ቅኑ መንገድም ምራን፤አንተ ቸር ነህና ደግ ደጉን ጨምርልን። ‹‹ተጠባባቂነትም በአላህ በቃ።›› [አልኒሳእ፡6]

እርሱ ተጠባባቂው በቂው አላህ ነው . .

ሁሉን ነገር ገላጩ አላህ . .

እርሱ ሁሉን ነገር ገላጩ አላህ ነው . . ‹‹አላህም እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ (ሁሉን ነገር) ገላጭ መኾኑን›› [አልኑር፡25]

ገላጭ የሆንከው አላህ ﷻ ሆይ! . . የእውነትን መንገድ ግለጥልን፤ከሐሰት መንገድ ጋር እንዳይደበላለቅብን አንተው ጠብቀን።

እውነትንና እውነታዎችን ሁሉ ገላጭ የሆነው አላህ ﷻ ፣በዚህም ጥርጣሬዎችን ሁሉ የሚያስወግድና የሚያጠራ ገላጭ ጌታ።

ተጋሪ የሌለው አንድ አምላክ መሆኑን የሚመለከተውን ተውሒድ ገላጭ የሆነ አላህ ﷻ ነው።

‹‹ሁሉን ነገር ገላጩ›› . . ስለ ቸርነቱ ስለ አንድነቱና ስለ ሥልጣኑ፣ አእምሯዊ ሸሪዓዊ ቁሳዊና ሕሊናዊ ማስረጃዎችን ያቀረበላቸው በመሆኑ ከፍጥረታቱ ያልተሰወረ፣ሁሉን ነገር ገላጩ ጌታ።

‹‹ሁሉን ነገር ገላጩ›› . . መልክተኛውን ﷺ በመላክና በገላጩ መጽሐፍ

ለባሮቹ እውነተኛውን ቀጥተኛ መንገድ ያሳየ ጌታ። ‹‹ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ።›› [አልማኢዳህ፡15]

የመታደልን መንገድ ለባሮቹ የገለጠ፣መታደልን እርሱን ከመታዘዝና ተውሒዱን ከማረጋገጥ ጋር ያቆራኘ ጌታ።

እርሱ ሁሉን ነገር ገላጩ አላህ ነው። . . .

ሁሉን ነገር ቻይ፣የችሎታ ባለቤት፣ቻዩ አላህ . .

እርሱ ሁሉን ነገር ቻይ፣የችሎታ ባለቤት፣ቻዩ አላህ ነው . . ‹‹አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።›› [አልበቀራህ፡284] , ‹‹(እነሱም ውድቅ ቃልና መውወንጀል በሌለበት) በውነት መቀመጫ ውስጥ፣ቻይ እሆነው ንጉሥ ዘንድ ናቸው።›› [አልቀመር፡55] , ‹‹እርሱ . . ቻይ ነው በላቸው።›› [አልአንዓም፡65]

‹‹በሁሉም ላይ ቻይ›› . . የብርቱ ችሎታ ባለቤት፣ባሻው ነገር ላይ ባሻው መንገድ ፍጹማዊ ችሎታ ያለው።

‹‹ሁሉን ቻይ›› . . ችሎታው የተሟላ፣የሚያኖርና የሚገድል። ፍጥረታትን ከምንም ፈጥሮ ያስገኘ። ያቀነባበራቸውና ያስተካከላቸው ሁሉን ቻይ።

‹‹ሁሉን ቻይ›› . . ችሎታው ምሉእ የሆነ፣በኃያል ችሎታው ፍጥረታትን ከምንም ያስገኘ። በችሎታው ነገሮቻቸውን ሁሉ ያቀነባበረ፣ያስተካከለና ያጸና። በችሎታው የሚያኖርና የሚገድል። ከሞት አስነስቶ ለሁሉም የሥራውን ዋጋ የሚሰጥ። በጎ ሠሪውን የሚሸልም፣ክፉ ሠሪውን የሚቀጣ። አንድን ነገር ሲሻ ኹን ሲለው የሚሆን። በኃያል ችሎታው ልቦችን እንዳሻውና ወደ ፈለገው መንገድ የሚገለባብጥ ጌታ።

‹‹ምንም የማይሳነው ሁሉን ቻይ›› . . በችሎታው ከሞት አስነስቶ የሥራን ዋጋ የሚሰጥ፣የልቦችን ዝንባሌ እንዳሻው የሚገለባብጥ።

‹‹ሁሉን ቻይ›› . . በምንም መልኩ እንከንና ጉድለት የማይጠናወተው የምሉእ ፍጹማዊ ችሎታ ባለቤት የሆነ።

‹‹ሁሉን ቻይ›› . . በፈለገው መንገድና በፈለገው ነገር ፍጥረታቱን የሚያቀነባብር፣ሁሉን ቻይ አምላክ።

እርሱ ምንም የማይሳነው ሁሉን ቻይ አላህ ነው . .

ወራሹ አላህ . .

እርሱ ወራሹ አላህ ነው . . ‹‹እኛም ሕያው የምናደርግና የምንገድል እኛው ብቻ ነን፤እኛም (ፍጡርን ሁሉ) የምንወርስ (ቀሪ) ነን።›› [አልሒጅር፡23]

‹‹ወራሹ›› . . ምድርንና በርሷ ላይ ያለውን ሁሉ የሚወርስ፣ከርሱ ﷻ በስተቀር ማንምና ምንም ቀሪ የማይኖር።

‹‹ወራሹ›› . . ግዛቱና ገዥነቱ ፍጹማዊ በመሆኑ ከፍጥረታቱ በኋላ ቀሪ የሆነ። ግፈኞችን፣እብሪተኞችንና አጥፊዎችን፣የሁሉም መመለሻ ወደርሱ ብቻ መሆኑንና ቀሪ ወራሽ እርሱ ብቻ መሆኑን በመንገር የሚያስጠነቅቅ እውነተኛው ወራሽ።

‹‹ወራሹ›› . . ገንዘብና ዕድሜ ተመላሽ የተውሶ ዕቃ በመሆናቸውና መመለሻው ወደ ወራሹ አላህ ﷻ ብቻ በመሆኑ፣በርሱ መንገድ ይለግሱ ዘንድ ባሮቹን የሚያበረታታ።

‹‹ወራሹ›› . . የጸጋዎች ሁሉ መነሻና መድረሻ እርሱ ብቻ በመሆኑ፣ምስጋና ቢስ እንዳይሆኑ ባሮቹን የሚያስጠነቅቅ ወራሽ ጌታ።

‹‹ወራሹ›› . . መሬትንና በላይዋ ያሉትን ሁሉ የሚወርስ። ሁሉም ሟችና አላፊ ሲሆን እርሱ ብቻ ቀሪና ወራሽ ነው። ‹‹እኛም (ከነሱ) ወራሾች ነበርን።›› [አልቀሶስ፡58]

እርሱ ወራሹ አላህ ነው . .

አላህ ሰሚው ተመልካቹ ነው . .

እርሱ ሰሚው ተመልካቹ አላህ ነው . .

አንተ ሰሚው ሆይ! ዱዓአችንን ስማልን፣ልመናችንን ተቀበል፤አንተ ሥራን ዎቻችንን፣ድክመታችንን፣በአንተ ላይ ብቻ ጥገኞች መሆናችንንም ትመለከታለህና።

‹‹ሰሚው አላህ›› . . ድምጾችን ሁሉ ደካማውንና ጯኺውንም የሚሰማ። አንዱ ድምጽ ከሌላው ድምጽ፣የአንዱ ጥያቄና ልመና የሌላውን ከመሰማት የማያውከው ሰሚው አላህ ﷻ ነው።

‹‹ተመልካቹ አላህ›› . . ትልቅም ይሁን ትልቅ፣ግልጽም ይሁን ስውር፣በቀንም ሆነ በሌሊት ሁሉንም ነገር የሚያይ ተመልካች ጌታ ነው።

‹‹ሰሚው›› . . ቋንቋዎችና ዘይቤዎቻቸው የተለያዩ ቢሆንም ሁሉንም ይሰማል።

‹‹ሰሚው ተመልካቹ›› . . የምትናገረውን ይሰማልና ራስህን መርምር ተቆጣጠር፤ጸሎትህን ያዳምጣልና ጌታህን ተማጸነው። ከርሱ የሚሰወር ምንም ነገር ስለሌለ ሥራህን ሁሉ ይመለከታልና በጎ በጎውን ሥራ፤እርሱ በጎ ሠሪዎችን ይወዳልና።

‹‹ተመልካቹ›› . . ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ሌሊት ጥቁር ጉንዳን ቋጥኝ ድንጋይ ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ይመለከታል፤ከሰባቱ ሰማያት በላይ ያለውን ሁሉ እንደሚያይ ከሰባት መሬቶች በታች ያለውንም ያያል።

‹‹ሰሚው ተመልካቹ›› . . ከርሱ የሚሰወር ምንም ነገር የለም፤ከእይታው የሚደበቅ መጪም ሆነ ሂያጅ የለም።

እርሱ ሰሚው ተመልካቹ አላህ ነው . .

አመስጋኙ አላህ . .

እርሱ አነስተኛ በጎ ሥራ የሚያመሰግን አመስጋኙ አላህ ነው . .

እርሱ አመስጋኙ አላህ ነው . . ‹‹አላህ አመስጋኝ ዐዋቂ ነውና።›› [አልበቀራህ፡158] ,‹‹ጌታችን በጣም መሓሪ አመስጋኝ ነውና።› [ፋጢር፡34]

እርሱ ﷻ ጥቂቱን መልካም ሥራ የሚያመሰግን፣ብዙውን ጥፋት የሚምር፣ሥራዎቻቸውን ለርሱ ፍጹም ላደረጉ ትጉሃን ባሮቹ ያለ ገደብ ምንዳ የሚሰጥ አመስጋኙ አላህ ነው።

‹‹አመስጋኙ አላህ›› . . ላመሰገነው ይሰጣል። ለለመነው የችሮታ እጁን ይዘረጋል። ያስታወሰውን ያስታውሰዋል፤ለአመሰገነ ሰው ይጨምርለታል። ጸጋውን ያስተባበለውን ለውድመት ያጋልጣል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦‹‹ብታመሰግኑም በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ፣ብትክዱም (እቀጣችኋለሁ)፤ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና።›› [ኢብራሂም፡7]

እርሱ ትንሹንም የሚያመሰግን አመስጋኙ አላህ ነው . .

ተመስጋኙ አላህ . .

እርሱ ተመስጋኙ አላህ ነው . . በርሱነቱ ተመስጋኝ፣በሥራዎቹም ተመስጋኝ፣በምግባሩም ተመስጋኝ፣በቃሎቹም ተመስጋኝ የሆነ አምላክ። በዩኒቨርሱ ውስጥ ከአላህ ﷻ በስተቀር ሌላ ተመስጋኝ የለም፤ምሉእ ምስጋና ምሉእ ውዳሴ ለርሱ ብቻ ነውና።

ተመስጋኙ አላህ . . በእርሱነቱ (በዛቱ)፣በስሞቹ፣በባሕርያቱና በሥራዎቹ ተመስጋኝ እርሱ ነው። ከስሞች መልካሞቹ፣ከባሕርያት ምሉእ የሆኑ፣ከሥራዎች ፍጹምና የጸኑ የሆኑ ያሉት አምላክ ነው። ሥራዎቹ ሁሉ በትሩፋትና በፍትሕ መካከል የሚሽከረከሩ ናቸው።

መጽሐፍህን ወደኛ በማውረድ ኃያልነትህን ስለ አሳወቅኸንና መልክተኛህን ሙሐመድ ﷺ ወደኛ ስለ ላክህ ምስጋና ለአንተ ይሁን።

እርሱ ተመስጋኙ አላህ ነው . .

የፍጥረታት ሁሉ የበላይ፣ትልቁ፣ታላቁ፣ባለ ግርማ ሞገሱ አላህ . .

የፍጥረታት ሁሉ የበላይ፣ትልቁ፣ታላቁ፣ባለ ግርማ ሞገሱ አላህ . .

እርሱ በዝና፣በአሸናፊነት፣በኩራት፣በኃያልነትና በታላቅነት ባሕርያት የሚገለጽ፣የፍጥረታት ሁሉ የበላይ፣ትልቁ፣ታላቁ፣ባለ ግርማ ሞገሱ አላህ ነው። የወዳጆቹንና የምርጥ አገልጋዮቹን ልብ ለግርማ ሞገሱ፣ለታላቅነቱ፣ለኃያልነቱ፣ለርሱ ባላቸው ተገዥነትና ተዋራጅነት የሞላ አላህ ﷻ ነው።

ኃያሉ ጌታ ላቀ!! የፍጥረታት ሁሉ የበላይ፣የታላቆች ሁሉ ታላቅ የሆነው አላህ ጥራት ተገባው!! ‹‹የታላቁንም ጌታህን ስም አወድስ።›› [አልዋቂዓህ፡96]

አንተ ኃያሉ የግርማ ሞገስና የክብር ባለቤት የሆንከው ጌታችን ሆይ! . . ምስጋና እና ውዳሴህን ቆጥሬን አንጨርሰውም።

በእርሱነቱ የልዕልና ባለቤት የሆነው፣በበስሞቹና በባሕርያቱ የልዕልና ባለቤት የሆነ ጌታ። ‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም።›› [አልሹራ፡11]

እርሱ የግርማ ሞገስና የኃያልነት ባለቤት ነው። አንዱንም ለኔ ይገባኛል ብሎ የተከራከረውን ሁሉ አከርካሪውን ይሰብረዋል። አላህ ﷻ ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ኩራት ኩታዬ ነው፤ታላቅነት ሽርጤ ነው፤አንዳቸውን የተሸማኝን ሰው ወደ እሳት አሽቀነጥረዋለሁ።›› (በአሕመድ የተዘገበ)

እርሱ የፍጥረታት ሁሉ የበላይ፣ትልቁ፣ታላቁ፣ባለ ግርማ ሞገሱ አላህ ነው . .

የሁሉ በላይ፣የላቀው የልዕልና ባለቤት አላህ . .

እርሱ የሁሉ በላይ፣የላቀው የልዕልና ባለቤት አላህ ነው . .

‹‹የሁሉ በላይ፣የላቀው የልዕልና ባለቤት›› . . በሁሉም መልኩ ፍጹማዊ ልዕልና ያለው፣በእርሱነቱ ፍጹማዊ ልቅና፣በባሕርያቱ ፍጹማዊ ልቅና፣በአስገዳጅ አንበርካኪነቱ የልዕልና ባለቤት የሆነ ጌታ። ‹‹እርሱም የሁሉ በላይ ታላቅ ነው።›› [አልበቀራህ፡255]

በዐርሹ ላይ ተደላድሏል፤በሁሉም የኃያልነት፣ የታላቅነት፣የግርማ ሞገስና የውበት ባሕርያት የሚገለጽ ፍጹማዊ ምሉእ አምላክ ሆኗል።

‹‹የሁሉ በላይ የላቀው›› . . ለርሱ ተገቢ ካልሆነ ነገር ሁሉ የላቀ፣ከእንከንና ከጉድለት ሁሉ የጠራ፣በእርሱነቱና በባሕርያቱ ከሁሉም በላይ የሆነ የልቅና ባለቤት።

እርሱ የሁሉ የበላይ፣የላቀው፣የልዕልና ባለቤት አላህ ነው . .

ያዡ ለቃቂው አላህ . .

እርሱ የሚጨብጠውና የሚዘረጋው አላህ ነው . .

‹‹ያዡ አላህ›› . . ከሕዝቦች ከከፊላቸው ሲሳይን ያዝ በማድረግ የሚፈትናቸው፣ሌሎቹን ይንበረከኩ ዘንድ ሲሳይን የሚከለክላቸው፣ሌሎቹን ደግሞ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ሲሳይ የሚያቆይባቸው ጌታ።

‹‹ለቃቂው አላህ›› . . ጥበቡ፣ቸርነቱ፣ደግነቱና ለጋሽነቱ በሚጠይቀው መሰረት ሲሳይን ለቀቅ አድርጎ የሚሰጥ፣ልቦችን በዕውቀት የሚቀልብ፣እጆቹን ዘርግቶ የሚለግስ ጌታ።

እርሱ የሚጨብጠውና የሚዘረጋው አላህ ነው . .

ሰጪው ነሺው አላህ።

እርሱ ሰጪው ነሺው አላህ ነው . .

ራሱን በራሱ እንደገለጸው ለሆነውና ፍጡራኑ ከሚገልጹት በላይ ለሆነው አላህ ምስጋና ይድረሰው።

ኢማም አሽሻፊዒ

‹‹ሰጪው ነሺው አላህ›› . . እርሱ የሰጠውን የሚከለክል፣እርሱ የከለከለውን የሚሰጥ የለም። ጥቅሞች ሁሉ የሚጠየቁትና የሚከጀሉት ከርሱ ነው። ለሚሻው ሰው የሚሰጠው እርሱ ነው፤በጥበቡና በእዝነቱ የሻውን ሰው የሚከለክልም እርሱ ነው።

የጸጋዎች ለጋሽ የሆንከው አላህ ሆይ! ከችሮታህ ለግሰን፤ከስጦታዎችህም ስጠን። አንተ ያዥ የሆንከው ጌታ ክፉውን ሁሉ ከኛ ያዝልን። ከልካይ የሆንከው ጌታ ክፉውንና እኩይ የሆነውን ሁሉ ከልክልልን።

እርሱ ሰጪው ነሺው አላህ ነው . .

   
Subscibe